Monday, August 8, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  መፍትሔ የሚሻው ጤናማ ያልሆነው ያንዳንድ የጤና ተቋማት የቆሻሻ አወጋገድ

  የአሥር ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረውን የኢትዮጵያ የአካባቢ ጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች ማኅበር በፕሬዚዳንትነት የሚመሩት አርጋው አምበሉ (ፕሮፌሰር) ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥር ከነበረው ከቀድሞ የጎንደር ሕክምና ሳይንስ ኮሌጅ በሳኒቴሽን በዲፕሎም ተመርቀዋል፡፡ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በኢንቫይሮመንታል ሔልዝ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ ከዚያም ወደ ቤልጂየም አቅንተው በጌት ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን አጠናቀዋል፡፡ በሥራ ዓለምም በጅማ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት፣ በጎዴ ሆስፒታል በሳኒቴሸን ባለሙያነት አገልግለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውኃና የኅብረተሰብ ጤና ክፍለ ትምህርት (የወተር ኤንድ ፐብሊክ ሔልዝ ዲፓርትመንት) የአካባቢ ጤና ፕሮፌሰር ናቸው፡፡  የቆሻሻ አወጋገድና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

  ሪፖርተር፡- የቆሻሻ አወጋገድ በምን መልኩ ነው የሚከናወነው?

  ፕሮፌሰር አርጋው፡- በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ የምፈልገው ነገር ቢኖር ቆሻሻ ሁለት ዓይነት መሆኑን ነው፡፡ የአንደኛው ዓይነት ቆሻሻ  ይህን ያህል አደጋ የማያስከትል ሲሆን፣ ሁለተኛው ዓይነት ቆሻሻ ደግሞ አደጋ የሚያስከትል ነው፡፡ ቆሻሻ ከሚመነጭበት ቦታ ከተወገደ በኋላ ለሌላው ችግር መፍጠር የለበትም፡፡ ብዙ ጊዜ ‹‹ከጓዳዬ ከተወገደ በኋላ ለሌላው አያገባኝም፤›› የሚለው የተሳሳተና አግባብ ያልሆነ አስተሳሰብ ጭራሽኑ መወገድ አለበት፡፡ ምክንያቱም ከጓዳህ የመነጨውን ቆሻሻ ሌላውን በሚጎዳ መልኩ ከተደፋ መልሶ እራስህን ጨምሮ ሊጎዳህ እንደሚችል መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ወይ ከውኃ ጋር አለበለዚያም በነፋስ ኃይል ተመልሶ ወደ ራስህ ቤት እንደሚመጣና የበሽታ አስተላላፊ የሆኑ የዝንብ መፈልፈያ እንደሚሆን ልብ ሊሉት ይገባል፡፡

  ሪፖርተር፡- አደገኛና አደገኛ ያልሆኑ ቆሻሻዎች ልዩነታቸውን ቢያብራሩት?

  ፕሮፌሰር አርጋው፡- ለጥያቄህ መልስ ከመስጠቴ በፊት የቆሻሻ ምንጮችን ብጠቅስልህ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም የቆሻሻ ምንጮች የከተማ እንዲሁም የኢንዱስትሪና የጤና ተቋማት ናቸው፡፡ ከዚህ በተረፈ ወደ አደገኛ ቆሻሻ ስንመጣ የችግሩ ግዝፈት እጅግ ከባድ ነው፡፡ ለአብነት ያህልም ከኢንዱስትሪ የሚለቀቁ የኤሌክትሮኒክስና ከጤና ተቋማት የሚወጡ የኢንፌክሽን ቆሻሻን (ዌስት) ማየት ይችላል፡፡ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያበቃላቸው የኮምፒዩተርና ሌሎች የኤሌክትሪክ ዕቃዎች ከደረቅ ቆሻሻ ጋር አብረው ሲጣሉ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ ይልቅ ዳግም አገልግሎት መስጠት (ሪሳይክል) እንዲችሉ ማድረግ፣ በዚህም ዙሪያ የአካባቢ ጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች ማኅበር በቅርበት ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ለማከናወን ማቀዱ ከወዲሁ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡ በተረፈ ከጤና ተቋማት የሚወጣው ቆሻሻ በከፍተኛ ደረጃ የጤና ጠንቅ ከመሆኑ ባሻገር ለፀረ ተዋህስያን መድኃኒት ያልተበገሩ ጀርሞችን የመፍጠር አቅም እንዳለው መታወቅ ይኖርበታል፡፡

  ሪፖርተር፡- እንዴት ነው ይህ የሚፈጠረው?

  ፕሮፌሰር አርጋው፡- በሕክምና ላይ ያለ ሰው መድኃኒት ይውጣል፡፡ መድኃኒቱ ደግሞ አልፎ አልፎ በተለያዩ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ተብላልቶ ይዋጣል (ሜታቦላይዝድ) ማለት አይደለም፡፡ የተወሰነ ይቀርና በሽንትና በሰጋራ መልክ ወደ ውጭ ይወጣል፡፡ በዚህ መልክ ወጥቶ አካባቢ ሲደርስ ይሰባበርና ሌላ አደጋ ለማድረስ በሚያስችለው መልክ ፀባዩን ይቀይራል፡፡ በዚህ ጊዜ ሌላ ተዋህስ ያገኝና መለማመድ ይጀምራል፡፡ በዚህም ፀረ ተዋህስያንን መቋቋም የሚችል ጂን ይፈጠራል፡፡ ጅኑ ደግሞ አንድ ተዋህስ ላይ ብቻ ተወስኖ አይቀርም፡፡ ወደ ሌላውም ይሸጋገራል፡፡ በዚህ መልኩ ለፀረ ተዋህስያን የማይበገሩ ጀርሞች እየተፈለፈሉ ይበዛሉ፡፡ ፀረ ተዋህስያን መድኃኒቶችን የተላመዱ ጀርሞች መፈጠራቸው በተጠቀሰው ዓይነት አካሄድ ብቻ አይደለም፡፡ የታዘዙ የፈውስ መዳኒቶችን በማቋረጥ፣ በአግባቡ አለመውሰድና ከሐኪም ትዕዛዝም ውጭም በመጠቀም ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- ጅን ማለት ምንድነው?

  ፕሮፌሰር አርጋው፡- ጅን ማለት የአንድን ተፈጥሮ የሚወስን ወይም ወሳኝ አካል ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- የፀረ ተህዋስያን መድኃኒት አጠቃቀማችን ምን እንደሚመስል መግለጽ ይቻላል?

  ፕሮፌሰር አርጋው፡- እንደ ኔዘርላንድስ በመሳሰሉ ያደጉ አገሮች ውስጥ የፀረ ተህዋስያን ጅን በጣም ትንሽ ነው፡፡ ምክንያቱም አንድ ታካሚ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው ፀረ ተህዋሱ የሚታዘዝለት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ማንም ሰው እንደፈለገው ነው ፀረ ተህዋስ የሚገዛውና የሚውጠው፡፡ እንዲያው በአጠቃላይ ትክክል ያልሆነ ወይም ሥርዓቱን ያልጠበቀ የመድኃኒት አጠቃቀም ኢትዮጵያ ውስጥ ተንሰራፍቶ ይታያል፡፡ ፀረ ተህዋስ መድኃኒቶች በተለያዩ መግቢያ በሮች በኮንትሮባንድ ወደ መሀል አገር ይገቡና በየሱቁ ይከማቻሉ፡፡ ሰዎች ሄደው እንደ ሸቀጥ ይሸምታሉ፡፡ ዶዙን አያውቁትም፡፡ በአግባቡም አይወስዱም፣ አንድ ቦታ ላይ ሲደርሱ ያቆሙታል፡፡

  ሪፖርተር፡- ቆሻሻዎችን ለማቃጠል ምን መሟላት አለበት ይላሉ?

  ፕሮፌሰር አርጋው፡- ሁሉም ቆሻሻዎች አይቃጠሉም፡፡ ቆሻሻን ለማቃጠል የሚያስችል የቆሻሻ ማቃጠያ ምድጃ መገንባት ይኖርበታል፡፡ ምድጃውም በዓለም አቀፍ ደረጃ የወጣውን መመዘኛ ማሟላት አለበት፡፡ መመዘኛውም ቆሻሻው ለማቃጠል የሚንቦገቦገው እሳት 800 ዲግሪ ሴሊሸልስ መድረስ አለበት፡፡ እሳቱ በተጠቀሰው መልኩ ካልነደደ ለመድኃኒት መያዣነት የሚያገለግሉት ልዩ ልዩ ዓይነት ብልቃጦችንና ጠርሙሶችን አመድ እስከሚሆኑ ድረስ ሊያቃጥላቸው አይችልም፡፡ ከዚህም ሌላ ማንደጃው ኦክስጅን ያለምንም ችግር ሊያስገባና አመድ ሊያስወጣ የሚያስችል ክፍል ሊኖረው ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የቆሻሻ ማቃጠያ ምድጃዎች ሁሉ ከፍ ብሎ የተጠቀሰውን ደረጃ ባሟላ መልኩ አልተሠሩም፡፡ በዚህም የተነሳ ቆሻሻው ወደ አመድነት እስከሚቀየር ድረስ በደንብ ሳይቃጠል ይቀርና እንደ ከሰል ሆኖ ይወጣል፡፡

  ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የሚገኙ የመንግሥትም ሆነ የግል ጤና ተቋማት ቆሻሻ አያያዛቸውንና አወጋገዳቸውን ማኅበሩ ለመመልከት ወይም ለመገምገም ሞክሯል?

  ፕሮፌሰር አርጋው፡- ሁሉንም ጤና ተቋማት እየተዘዋወርን አልተመለከትንም፡፡ በጣም ጥቂቶቹን ግን አይተናል፡፡ ካየናቸው አንዳንዶቹ አወጋገዳቸው ጤናማ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ የሚያመነጩትን ቆሻሻ ካከሙ በኋላ አይደለም እንዲፈስ የሚያደርጉት፡፡ ከከተማው ቆሻሻ ጋር አንድ ላይ እንዲፈስ ነው የሚያደርጉት፡፡ ይሄ ደግሞ በጣም ትልቅ ስህተት ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- ለቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ብቸኛ መፍትሔው ምንድነው ይላሉ?

  ፕሮፌሰር አርጋው፡- ይህ ጉዳይ ለአንድ መንግሥታዊ አካል ላይ ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ ኅብረተሰቡም ኃላፊነቱን በሚገባ እየተወጣ ጤናማ አካባቢ ለመኖር ዝግጁ መሆን አለበት፡፡ ከእኔ ጋ የሚመነጨውን ቆሻሻ ከጓሮዬ ካስወገድኩ ለሌላው ግድ የለኝም የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት ማረም አለበት፡፡ የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ በተደራጀና በተቀናጀ መልክ ማስኬድ አለበት፡፡ በተረፈ የቆሻሻ ማከሚያ ቦታዎችን ማዘጋጀት የመንግሥት ኃላፊነትና ግዴታ ነው፡፡ የአካባቢ ጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች ማኅበርም የማስገንዘብ ሥራ ማከናወንና የተሻሻሉ የደረቅ ቆሻሻ ማቃጠያ ቴክኖሎጂዎችን የማስተዋወቅ ሥራ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን ማኅበሩ ሁሉን አቀፍ ጥረት በማድረግ ላይ ነው፡፡

   

   

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  የዩኒቨርሲቲ መምህራን ከደመወዝ ጭማሪና ከዕርከን ዕድገት ጋር በተያያዘ መንግሥትን አስጠነቀቁ

  ‹‹የደመወዝ ጉዳይ የትምህርት ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንም...

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የውጭ አገር ሕክምና የሚያስፈልጋቸውን እንግልት ለመቀነስ

  በኢትዮጵያ የሕክምና አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ችግር እንዳለ ይታመናል፡፡ በተለይም በሕክምና ስህተት ሕሙማን ለሞት ሲጋለጡ አልያም ደግሞ ለሌላ ስቃይ ሲዳረጉም ይታያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በዝቅተኛ...

  አሠሪና ሠራተኛ የሚገናኙበት ዓውደ ርዕይ

  በአዲስ አበባ ከተማ 23 ሚሊዮን ወጣቶች እንደሚኖሩ ከዓመት በፊት ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡ ከዚህ ውስጥ መሥራት የሚችሉ ወይም ዕድሜያቸው ለሥራ የደረሱ 75...

  የጎዳና ሕይወትን ለመከላከል የአንበሳውን ድርሻ መያዝ ያለበት ማነው?

  ማስተር ኤርሚያስ ገሠሠ የጳጉሜን አምስት ግብረ ሠናይ ድርጅት መሥራች ሥራ አስኪያጅና የማርሻል አርት አሠልጣኝ ናቸው፡፡ የግብረ ሠናይ ድርጅታቸውን እንቅስቃሴ አስመልክቶ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- የጳጉሜ...