Monday, August 8, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  ጥብቅናን በማኅበር

  ሕግና ሥርዓት እንዲተገበር ከሚያግዙ ባለድርሻዎች መካከል የጥብቅና አገልግሎት ተጠቃሽ ነው፡፡ ጠበቆች አገልግሎታቸውን በድርጅት ወይም ማኅበር አማካይነት ለመስጠት ቢፈልጉም፣ ከሕግ አግባብ አኳያ ተግባራዊ ማድረግ እንዳልቻሉ ይገልጻሉ፡፡ በ1992 ዓ.ም. እንደወጣ የሚነገርለት አዋጅ ቁጥር 199፣ የጥብቅና ፈቃድና አስተዳደር አዋጅ፣ የጥብቅና ማኅበር መመሥረት እንደሚችል ቢገልጽም፣ ለዚህ አዋጅ ዝርዝር መመርያ ይወጣል በማለት ይዘጋዋል፡፡ በሐምሌ 2013 ዓ.ም. የወጣው አዲሱ የፌዴራል የጥብቅና አገልግሎት ፈቃድ አሰጣጥና አስተዳደር አዋጅ 249 ደግሞ፣ መመርያ ቀመስ የሚመስሉ ዝርዝር ድንጋጌዎችን በውስጡ የያዘ መሆኑ ከቀድሞ አዋጅ የተሻለ ያደርገዋል፡፡ ከአገልግሎት ሰጪ የፍትሕ አካላት ውስጥም ማኅበር ለመመሥረትና አገልግሎት ለመስጠት እንቅስቅሴ የጀመሩ እንዲሁም የመሠረቱ አሉ፡፡ ከመሠረቱት ውስጥ የሐበሻ ጥብቅና አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማኅበር  ይገኝበታል፡፡ አቶ ውብሸት ደምሴ የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ሔለን ተስፋዬ አነጋግራቸዋለች፡፡

  ሪፖርተር፡- የማኅበሩ መመሥረት የፍትሕ ሥርዓቱን ከማገዝ አኳያ ምን ጠቀሜታ ይኖረዋል?

  አቶ ውብሸት፡- ሐበሻ የጥብቅና አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክና ማኅበር የተቋቋመው መጋቢት 28 ቀን 2014 ዓ.ም. ነው፡፡ የዚህ ማኅበር መሥራቾች እኔን ጨምሮ አምስት ነን፡፡ ለብዙ ዓመታት በጥብቅና አገልግለናል፡፡ ማኅበር በመሆናችን በሥራችን ብዙ ተቀጣሪዎች የሥራ ዕድል ያገኛሉ፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱን በሚያግዝ በአግባቡ በተጠና ሁኔታ ለመሥራት እንደ ማኅበር መሆናችን በእጅጉ ጠቃሚ ነው፡፡ በሌላ በኩል ስፔሻላይዝድ ያደረጉ ጠበቆች በማኅበሩ ውስጥ በመኖራቸው፣ የደንበኞችንና የፍርድ ቤት ሥርዓትን ቀላል ያደርገዋል፡፡ በእኛ አገር የደንበኛን ጉዳይ ከሁለት በላይ ጠበቆች እንዳያዩት ስለሚደረግ ብዙ ክፍተቶችን ይሞላል ብለን እናስባለን፡፡ በዋነኛነት ተቋም ሲኮን ተጠያቂ ለመሆንና ኃላፊነት ለመውሰድ ያስችላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ግለሰብ ቅሬታ ቢያቀርብ በቀጥታ ወደ ማኅበሩ ይደርሳል፡፡ ነገር ግን ጠበቃው ለብቻው የሚሠራ ቢሆን በቀላሉ ለማግኘት ሊያስቸግር ስለሚችል እንደ ማኅበር መሆኑ ለባለጉዳዮች ብዙ ጠቀሜታዎች ይኖሩታል፡፡ በማኅበር መሥራት በሌሎች አገሮች የተለመደ ነው፡፡ ጠበቆችም በአንድ ጉዳይ ላይ እስፔሻላይዝ እንዲያደርጉ ዕድል ከመስጠት በተጨማሪ ባለጉዳዮችም ጉዳዩን የሚያውቅ ባለሙያ ለማግኘት አይቸገሩም፡፡

  ሪፖርተር፡- እንደ ማኅበር መሆናችሁ ለባለጉዳይ ምን ዓይነት ጠቀሜታ ይኖረዋል?

  አቶ ውብሸት፡- ለምሳሌ የውጭ አገር ኢንቨስተር ከግለሰብ ጠበቃ ጋር ውል ለማድረግ የሚገደደው የጥብቅና ድርጅት ባለመኖሩ ነው፡፡ ነገር ግን አገልግሎቱ በድርጅት መልክ መምጣቱ፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ባለው፣ የተደራጀና የተለያዩ ዕውቀትና ልምድ ባላቸው ጠበቆች ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል፡፡ አገልግሎቱ በማኅበር ደረጃ መምጣቱ ኢንቨስትመንትን ያበረታታል፡፡

  ሪፖርተር፡- በ1992 ዓ.ም. የወጣው አዋጅ የጥብቅና አገልግሎት ለመመሥረት አሠሪ የሆኑ ጉዳዮች እንዳሉት ተናግረዋል፡፡ የአሁኑ ወይም አዲሱ አዋጅስ ምን ጠቀሜታዎች አሉት? ምን ዓይነት ችግሮች ይገጥሙናል ብላችሁ ትጠብቃላችሁ?

  አቶ ውብሸት፡- አዲሱ አዋጅ ዝርዝር መመርያዎች በመያዙ ማኅበራን በተገቢ መንገድ ለማደራጀት ያስችላል፡፡ በሌላ በኩል ከዚህ በኋላ ብዙ ማኅበራት እንዲቋቋሙ ከማገዙ በተጨማሪ ለባለጉዳዮች አማራጮችን ያስገኛል፡፡ ማኅበራት ወይም ድርጅቶች እንዳይበዙ ከሚያደርጉ ችግሮች መካከል መንግሥታዊ አገልግሎቶች ከዚህ ጋር የሚጣጣሙበት አሠራር አለመኖሩ ነው፡፡ ጥብቅና በባህሪው ንግድ አይደለም፡፡ ጥብቅና አገልግሎት ነው፡፡ ሙያዊ ስለሆነ ማኅበረሰቡን በፍትሕ ተደራሽ ከማድረግ ረገድ ከኪሳራ ተጠብቀው ማገልገል ስላለባቸው ግብር አመጣጠኑ ወደፊት ከምንጠብቃቸው ፈተናዎች አንዱ ነው፡፡ የጥብቅና አገልግሎት ላይ ታክስና ተርን ኦቨር ታክስን በተመለከተ ሙያው የቅንጦት ዘርፍ ባለመሆኑ፣ በመንግሥት በኩል ይታያል ብለን እናስባለን፡፡

  ሪፖርተር፡- ስለ ክፍያ ከተነሳ በጥብቅና አገልግሎት ክፍያችሁ ከፍተኛ እንደሆነ ተገልጋዮች ይናገራሉ፡፡ በዚህ ረገድ ማኅበራችሁ ይዞ የመጣው ነገር ይኖር ይሆን?

  አቶ ውብሸት፡- የጠበቃ ዋጋ ከሁሉም አገልግሎት ያነሰ ነው፡፡ በውጤት ደረጃ ግን ከማንኛውም ዘርፍ በላይ ኃላፊነት አለበት፡፡ የአንድ ጠበቃ የአገልግሎቱ ዋጋ በሕግ የተወሰነ ነገር ባይኖረውም፣ እንደ ልምድ ንብረት ከሆነ ከመቶኛ አሥር በመቶ ድረስ ለጠበቃው ይሰጣል፡፡ ይህ ማለት ልማድ ነው፡፡ ለምሳሌ ኦሮሚያ ክልል የንብረት ጉዳይ ላይ ጠበቃው የሚያገኘው 15 በመቶውን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ዋጋው ውድ አይደለም፡፡ የጥብቅና ድርጅት መምጣቱ ምን ጥቅም አለው? ካልሽ ለምሳሌ ድሮ በነበረኝ ልምድ በፍትሐ ብሔር ጉዳይ ወደ እኔ ከመጣ አሳልፌ ለሌላ ጠበቃ እሰጣለሁ፡፡ አሁን ግን የትኛውም ጉዳይ ወደ ድርጅታችን ከመጣ ከጉዳዩ አንፃር የሚፈልጓቸውን ባለሙያዎች ያገኛሉ፡፡ ከዋጋም አንፃር ቢሆን በማኅበር ሲሆን የሚሰጠው ጠቀሜታ አለው፡፡ ድርጅቱ ለነገ መልካም ስሙ ሲል በአንድ ውል መሥራት ያለበትን ያውቃል፡፡ የጠበቆች ዋጋ አይቀመስም የተባለው በእያንዳንዱ የጉዳይ ምልልስ አሥር በመቶ ስለሚከፍሉ ነው፡፡

  በማኅበር ሲሆን፣ ለአንድ ጉዳይ አንድ ጊዜ ብቻ እንዲከፍሉ ይደረጋል፡፡ ከሥነ ምግባር ውጪ የሆኑ ጉዳዮች ሲኖሩ በግለሰብ ሲሆን አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ድርጅት ሲሆን በሕግና በመመርያ ስለሚሠሩ ደንበኞች ብዙም ችግሮች አይገጥሟቸውም፡፡ በድርጅት መሆኑ ሌላኛው ጠቀሜታ አንድ ደንበኛ በድርጅቱ ምክንያት ችግር ቢገጥመው በኢንሹራንሱ መሠረት የሚካስ ይሆናል፡፡ ከዚህ ቀደም በሕግ የተቀመጠ ነገር ቢኖርም፣ ብዙም ተግባራዊ አልተደረገም፡፡ ድርጅት ሲሆን ግን የግድ ተጠያቂነት ስለሚኖር ሕጉ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡

  ሪፖርተር፡- ሐበሻ የጥብቅና አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የሽርክ ማኅበር ምን ያህል የሥራ ዕድል ይከፍታል?

  አቶ ውብሸት፡- ድርጅታችን አዲስ ስለሆነ ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ የሥራ ዕድል ይኖራል ብለን እናምናለን፡፡ ፈቃድ ያላቸውን ጠበቆች፣ ልምድ ያላቸውንና አዲስ ተመራቂ ተማሪዎችን ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር እየተነጋገርን እንቀጥራለን፡፡ በኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜያት በክልል ከተሞችም ተደራሽ ለመሆን ህልም አለን፡፡ በዚያ መሠረት የሚያስፈልገን የሰው ኃይል ብዙ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ሌሎችም ወደዚሁ ማኅበር ማስገባት ይጠበቅብናል፡፡ የአገር ውስጥ የጥብቅና አገልግሎት ከመስጠት በተጨማሪ ከአገር ውጪ ያሉ ጉዳዮችን የመቃኘት ትልም አለን፡፡ ከኢትዮጵያ ውጪ የሚገኙ አገሮች ጋር የጥብቅና ኔትወርኪንግ አለን፡፡ ለዚህም የጥብቅና አገልግሎት የሚሰጠው በበይነ መረብና በመደበኛ ይሆናል፡፡ በዋናነት የጥብቅና አገልግሎት የምንሠራው ኮርፖሬት ቢዝነስ ላይ ነው፡፡ ከኢንቨስትመንት፣ ድርጅት መመሥረትና ሌሎችን ጉዳዮች በሕግ አግባብነት ላይ ከተለያዩ ተቋሞች ጋር መሥራት እንፈልጋለን፡፡ ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሕግ አገልግሎት ተደራሽ መሆን ስላለበት ማኅበሩ ማኅበራዊና አገራዊ ጉዳዮች ላይ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ማኅበራዊ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ የምሠራ ሲሆን፣ አቅም ለሌላቸው ዜጎች ነፃ የጥብቅና አገልግሎት በመስጠት አገራዊ ኃላፊነታችን እንወጣለን፡፡

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  የዩኒቨርሲቲ መምህራን ከደመወዝ ጭማሪና ከዕርከን ዕድገት ጋር በተያያዘ መንግሥትን አስጠነቀቁ

  ‹‹የደመወዝ ጉዳይ የትምህርት ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንም...

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የውጭ አገር ሕክምና የሚያስፈልጋቸውን እንግልት ለመቀነስ

  በኢትዮጵያ የሕክምና አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ችግር እንዳለ ይታመናል፡፡ በተለይም በሕክምና ስህተት ሕሙማን ለሞት ሲጋለጡ አልያም ደግሞ ለሌላ ስቃይ ሲዳረጉም ይታያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በዝቅተኛ...

  አሠሪና ሠራተኛ የሚገናኙበት ዓውደ ርዕይ

  በአዲስ አበባ ከተማ 23 ሚሊዮን ወጣቶች እንደሚኖሩ ከዓመት በፊት ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡ ከዚህ ውስጥ መሥራት የሚችሉ ወይም ዕድሜያቸው ለሥራ የደረሱ 75...

  የጎዳና ሕይወትን ለመከላከል የአንበሳውን ድርሻ መያዝ ያለበት ማነው?

  ማስተር ኤርሚያስ ገሠሠ የጳጉሜን አምስት ግብረ ሠናይ ድርጅት መሥራች ሥራ አስኪያጅና የማርሻል አርት አሠልጣኝ ናቸው፡፡ የግብረ ሠናይ ድርጅታቸውን እንቅስቃሴ አስመልክቶ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- የጳጉሜ...