Monday, August 8, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  የዝቅተኛ የኅብረተሰብ ክፍሎች የፋይናንስ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ

  አንዳንድ ተቋማት ያሉባቸውን ክፍተቶች በማረም ለተገልጋይ ግልጽ፣ ፈጣንና ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓት በመዘርጋት አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ የፋይናንስ ተቋማት ዘመናዊ አሠራር በመዘርጋትና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለደንበኞቻቸው የሚሰጡትን አገልግሎት እያዘመኑም መጥተዋል፡፡ የሸገር የገንዘብ ቁጠባና ብድር መሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበር በቴክኖሎጂ ራሳቸውን እያዘመኑ ከሚገኙ የገንዘብ ተቋማት አንዱ ነው፡፡ በቅርቡም ሦስት የቴክኖሎጂ ውጤቶችን አስጀምሯል፡፡ የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን ለአባላቱ ከማስተዋወቅ በተጨማሪ፣ መረጃን በተደራጀ መንገድ ለመያዝና ማንኛውንም አገልግሎት በኦንላይን ለመስጠት የሚያስችሉ የአባላት ፖርታል፣ የሞባይል መተግበሪያና ድረ ገጽ አስጀምሯል፡፡ አቶ ቁምነገር ማስረሻ የሸገር የገንዘብ ቁጠባና ብድር መሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበር ሰብሳቢ ናቸው፡፡ ተቋሙ ባስጀመረው ቴክኖሎጂ ዙሪያ ሔለን ተስፋዬ አነጋግራቸዋለች፡፡

  ሪፖርተር፡- ሸገር ያስተዋወቀው ቴክኖሎጂ ምንድነው?

  አቶ ቁምነገር፡- ሸገር የኅብረት ሥራ ማኅበር ላይ ማዕከል ያደረገ የፋይናንስ ተቋም ነው፡፡ ማይክሮ ፋይናንስ ከባንክ የሚለዩባቸው የራሳቸው የሆኑ ነገሮች አላቸው፡፡ በኅብረት ሥራ ኤጀንሲ አዋጅና መመርያ መሠረት የምንሠራ ሲሆን፣ ያስተዋወቅነውም  የአባላት ፖርታል፣ ድረ ገጽና መተግበሪያዎችን ነው፡፡ በዋናነት በወረቀት ስንሠራ የነበረውን ወደ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ቀይረናል፡፡ አሠራራችንን በቴክኖሎጂ የታገዘ አድርገን እሩቅ ያሉ አባሎቻችን በሞባይላቸው በቀላሉ ክፍያን እንዲፈጽሙ፣ እንዲቆጥቡ፣ ብድር ማግኘትና ስለራሳቸው መረጃ ማወቅ እንዲችሉ ለማድረግ ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- በቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራር ማቅረባችሁ ለሸገርም ሆነ ለሌሎች የገንዘብ የሚመጡ ማኅበራት ምን ጠቀሜታ ይኖረዋል?

  አቶ ቁምነገር፡- ከሌሎች ማኅበራት ጋር ልምድ ልውውጥ እናደርጋለን፡፡ አባላት በቀላሉ ቴክኖሎጂውን በሞባይላቸው ተጠቅመው አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል፡፡ ገንዘብ በማንኛውም ባንክ አስተላልፈው ደረሰኛቸውን በሲስተሙ አማካይነት ማግኘት ይችላሉ፡፡ የግድ ቢሮ መምጣት አያስፈልጋቸውም፡፡ ሌሎች ማኅበራትም ቴክኖሎጂዎቹን በመጠቀም ሥራቸውን ቀላል ማድረግ ይችላሉ፡፡ ብድር ሲጠይቁ መጠኑን በእነዚህ ቴኖሎጂዎች አማካይነት መጠየቅ ይችላሉ፡፡ በሲስተሙ አማካይነት የክፍያዎቻቸውን፣ የብድርና የሌሎች አገልግሎቶችን መረጃዎች በቀላሉ መሰነድ ያስችላል፡፡ ሌሎች ተቋማት በእኛ አሠራር መሠረት የራሳቸውን የቴክኖሎጂ ሥርዓት እንዲያበለፅጉ ሒደቱን ቀለል ያደርግላቸዋል፡፡ እኛ ለሙከራና መሰል ሥራዎች ያሳለፍነው ውጣ ውረድ እነሱ ላይ እንዳይደገም ዕድል ይሰጣል፡፡  

  ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ከሌሎች ማኅበራት ምን የተለየ አሠራር ይዞ ብቅ ብሏል?

  አቶ ቁምነገር፡- የኅብረት ሥራ የገንዘብ፣ ቁጠባና ብድር ማኅበራት በሌሎች አገሮች ለምሳሌ በባንግላዴሽ፣ ህንድና ኬንያ በኢኮኖሚው ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ አምጥተዋል፡፡ በየአገሮቹ ዓመታዊ ጠቅላላ ምርት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያመጡት እነዚህ ማኅበራት ናቸው፡፡ የኬንያን ኢኮኖሚ ብንመለከት ለዓመታዊ ጠቅላላ ምርት ከ45 በመቶ በላይ  አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በኢትዮጵያ ምን ያህል እንደሆነ ባይታወቅም፣ የማኅበራቱ አስተዋጽኦ የሚናቅ አይደለም፡፡ በሌሎች አገሮች የጤና ባለሙያዎች፣ የመምህራን ማኅበራት ወጥ የሆነ አሠራር ስላላቸው ለኢኮኖሚው የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ይታወቃል፡፡ በእኛ አገር የገንዘብ ብድርና ቁጠባ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ጠቀሜታ በደንብ ባለመታወቁ፣ ለኢኮኖሚው ያላቸው አስተዋጽኦ አይታወቅም፡፡ ሸገር ሲመሠረት በመመርያና ደንብ የተብራራ ኃላፊነት እንዲኖረውና አሠራሩ እንዲዘምን በማድረግ፣ ተቋሙን ለመጠበቅ፣ ተራማጅ ለማድረግ የአባላቱን ፍላጎት ለማሟላት የአገልግሎት ዕድል በማቻቸት ማሻገር መቻሉ ከሌሎች ለየት ያደርገዋል፡፡

  ሪፖርተር፡- ኅብረት ሥራ ማኅበራት በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የሚጠቅሙ ናቸው፡፡ ማኅበሩ እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች በምን መልኩ እየጠቀመ ይገኛል?

  አቶ ቁምነገር፡- ማይክሮ ፋይናንስ በተለይ በመካከለኛና ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚጠቅም ነው፡፡ ለምሳሌ ሸገር ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ሆነው መክፈል የማይችሉ ዜጎችን በሁለት ሺሕ ብር አሥር ዕጣ እንዲገዙ በ1,000 ብር እንዲመዘገቡ ያደርጋል፡፡ ይህን መክፈል ለማይችሉ ደግሞ የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የሚሠሩ ተቋማትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማስተባበር መግቢያ እንዲከፍሉላቸው፣ ሥልጠና እንዲያገኙ፣ ሪቮልቪንግ ፈንድ እንዲያገኙ ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምረናል፡፡ ይህ ገና አንድ ዓመት በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ አላደረግነውም፡፡ ዋናው የማኅበራችን ዓላማ ግን እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ማድረግ ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- የሰነድ መጥፋት የብዙ ዘርፎች ችግር ነው፡፡ ይህንን ለመከላከል ምን እየሠራችሁ ነው?

  አቶ ቁምነገር፡- የሰነድ መጥፋት የብዙዎች ችግር ነው፡፡ እንደ ሸገር የገንዘብ ብድርና ቁጠባ ኅብረት ሥራ ማኅበር ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም የግድ ነው ብለን በመረዳት ወደ ሥራ ገብተናል፡፡ ሁሉንም ሥራ በቴክኖሎጂ ታግዘን ከሠራን መረጃዎች እንዳይጠፉ ያግዘናል፡፡ ተጠያቂነትም ለማስፈን ቴክኖሎጂ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ተጠያቂነት ያለው አሠራር እንዲኖር በቴክኖሎጂ መታገዝ ያስፈልጋል፡፡  

  ሪፖርተር፡- በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ምን ያህል አባላትን አፈራችሁ?

  አቶ ቁምነገር፡- በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ1,500 በላይ አባላት አፍርተናል፡፡ በመጪዎች ዓመታት ውስጥ የአባላትን ቁጥር በማብዛት ተቋሙንም አባላቱንም ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ማድረግ ዓላማችን ነው፡፡

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  የዩኒቨርሲቲ መምህራን ከደመወዝ ጭማሪና ከዕርከን ዕድገት ጋር በተያያዘ መንግሥትን አስጠነቀቁ

  ‹‹የደመወዝ ጉዳይ የትምህርት ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንም...

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የውጭ አገር ሕክምና የሚያስፈልጋቸውን እንግልት ለመቀነስ

  በኢትዮጵያ የሕክምና አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ችግር እንዳለ ይታመናል፡፡ በተለይም በሕክምና ስህተት ሕሙማን ለሞት ሲጋለጡ አልያም ደግሞ ለሌላ ስቃይ ሲዳረጉም ይታያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በዝቅተኛ...

  አሠሪና ሠራተኛ የሚገናኙበት ዓውደ ርዕይ

  በአዲስ አበባ ከተማ 23 ሚሊዮን ወጣቶች እንደሚኖሩ ከዓመት በፊት ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡ ከዚህ ውስጥ መሥራት የሚችሉ ወይም ዕድሜያቸው ለሥራ የደረሱ 75...

  የጎዳና ሕይወትን ለመከላከል የአንበሳውን ድርሻ መያዝ ያለበት ማነው?

  ማስተር ኤርሚያስ ገሠሠ የጳጉሜን አምስት ግብረ ሠናይ ድርጅት መሥራች ሥራ አስኪያጅና የማርሻል አርት አሠልጣኝ ናቸው፡፡ የግብረ ሠናይ ድርጅታቸውን እንቅስቃሴ አስመልክቶ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- የጳጉሜ...